Download this Blogger Template by Clicking Here!

Ad 468 X 60

Monday 25 August 2014

Widgets

ተየሙም



ትምህርት ቁጥር 1

                                       ተየሙም

ተየሙም ማለት የዓረብኛ ቋንቋ ትርጉሙ መፈለግ ማለት ሲሆን ሸሪዓዊ ትርጉሙ አላህን ለማምለክ በንፁህ መሬት ሸሪዓው በደነገገው መልኩ እጅና ፊትን ማበስ ማለት ነው፡፡
የተየሙም ሸሪዓዊ ድንጋጌና ማስረጃው:-
ተየሙም አላህ ለባሮቹ ገር ያደረገው ድንጋው ሲሆን የነብዩ ህዝቦች ከሌላው የሚለዩበት መለያ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ወደ ሶላት በቆማችሁ (ለመቆም ባሰባችሁ) ጊዜ ፊቶቻችሁን፣ እጆቻችሁንም እስከ ክርኖች እጠቡ፡፡ ራሶቻችሁንም (በውሃ) አብሱ፡፡ እግሮቻችሁንም እስከ ቁርጭምጭሚቶች (እጠቡ)፡፡ (ሴት ጋር በመገናኘት ወይም በሌላ ምክንያት «ጀናባ») ብትኾኑ (ገላችሁን) ታጠቡ፡፡ በሽተኞች ወይም በጉዞ ላይ ብትኾኑም ወይም ከእናንተ አንዳችሁ ከዓይነ ምድር ቢመጣ ወይም ሴቶችን ብትነካኩና ውሃን ባታገኙ ንጹሕን የምድር ገጽ አስቡ ፡፡ ከሱም ፊቶቻችሁንና እጆቻችሁን አብሱ፡፡ አላህ በእናንተ ላይ ምንም ችግር ሊያደርግ አይሻም፡፡ ግን ታመሰግኑ
ዘንድ ሊያጠራችሁና ጸጋውን በእናንተ ላይ ሊሞላ ይሻል፡፡››
(አል ማኢዳህ 6)

ነብዩም (ሠለላሁ ዓለይሒ ወሠለም) እንዲህ ብለዋል
“ውሃ ለአስር አመታት ባታገኝ እንኳን ንፁህ መሬት በቂህ ነው፡፡ ውሃ ስታገኝ ግን ገላህን አስነካው፡፡”(አቡዳውድና ቲርሚዚይ ዘግበውታል)
በሌላም ሀዲስ እንዲህ ብለዋል
“መሬት ለእኔ መስገጃና ጠሃራ ማድረጊያ ተደርጎልኛል፡፡”
(ቡኻሪና ዘግበውታል)
ተየሙም መስፈርቶቹ ከተሟሉ በሸሪዓው የተፈቀደ ስለመሆኑና የውሃን ጠሃራ ተክቶ በውሃ ጠሃራ ሊሰሩ የሚችሉ ለምሳሌ ሰላት፣ ካዕባን ጠዋፍ ማድረግ፣ ቁርአን ማንበብና ሌሎችም በተየሙም ሊፈፀሙ እንደሚችሉ ዑለማዎች ሁሉም ተስማምተውበታል፡፡
በመሆኑም ተየሙም ሸሪዓዊ ድንጋጌ ስለመሆኑ ቁርአን ሀዲስና የኡለማዎች ስምምነት (ኢጅማዕ) መረጃ ሊሆኑ ችለዋል ማለት ነው፡፡

                                     ትምህርት ቁጥር 2

                         #የተየሙም_መስፈርቶችና_እንዲፈቀድ_የሚያደርጉ_ምክንያቶች


የተየሙም መስፈርቶችና እንዲፈቀድ የሚያደርጉ ምክንያቶች
ውሃን በማጣት ወይም ህመምን ወይም ደግሞ ከባድ ብርድን በመፍራት ውሃን መጠቀም ካልተቻለ ተየሙም ማድረግ ይፈቀዳል፡፡ ለዚህ ማስረጃ ዒምራን ኢብን ሁሰይን ባስተላለፉት ሀዲስ ነብዩ (ሠለላሁ ዓለይሒ ወሠለም) እንዲህ ብለዋል “ንፁህ በሆነ መሬት ተየሙም ካደረግክ በቂ ነው፡፡” ወደፊት በዚህ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ ይኖረናል፡፡

ተየሙም ትክክለኛ እንዲሆን የሚከተሉትን መስፈርቶች ሟሟላት ይኖርበታል፡፡
1. ኒያህ፦ ሰላትን ለመስገድ እንዲያስችል በልብ ማሰብ ማለት ሲሆን ኒያ በሁሉም የአምልኮ ስርዓቶች ላይ መስፈርት ነው፡፡
2. ሙስሊም መሆን፦ ካፊር ተየሙም ቢያደርግ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም ተየሙም ዒባዳ (አምልኮ) ነው፡፡
3. አዕምሮ ጤናማ መሆን፦ አዕምሮውን ያጣ ለምሳሌ በእብደት ወይም በአዙሪት ራሱን የሳተ ተየሙሙ ትክክል አይሆንም፡፡
4. የመለየት እድሜ የደረሰ፦ ከሰባት አመት በታች ከሆነ ተየሙሙ ትክክል አይሆንም፡፡
5. ውሃ ማጣት፦ አላህ እንዲህ ብሏል፡-
‹‹ውሃን ባታገኙ ንጹሕን የምድር ገጽ አስቡ›› (አል ማኢዳህ 6)
ነብዩም (ሠለላሁ ዓለይሒ ወሠለም) እንዲህ ብለዋል
“አስር አመት እንኳን ውሃ ቢያጣ የሙስሊም መፅጂያ ተየሙም ነው፡፡ ውሃ ካገኘ ግን አካሉን ያስነካው ይህ ለእርሱ የተሻለ ነው፡፡” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
ውሃን በመጠቀሙ ህመሙ የሚባባስ ወይም ፈውሱን የሚያዘገየው ከሆነም ውሃን ትቶ ተየሙም ማድረግ ይችላል፡፡
አላህ እንዲህ ብሏል፡-
“በሽተኞች ብትኾኑ”
ነብዩም (ሠለላሁ ዓለይሒ ወሠለም) በቁስሉ ምክንያት ስለሞተው ሰው እንዲህ ብለዋል
“ገደሉት አላህ ይግደላቸውና ካላወቁ አይጠይቁም እንዴ? ያለማወቅ መድኃኒት እኮ መጠየቅ ነው፡፡”
እንዲሁም ውሃን ከተጠቀመ የሚጐዳው የሆነ ከባድ ብርድ ቢኖርም ተየሙም ማድረግ ይቻላል፡፡ ለዚህ ማስረጃ ዓምር ኢብን አል ዓስ “ለዛቲ ሰላሲል” ዘመቻ በተላከበት የገጠመውን ሲናገር እንዲህ ይላል “በአንድ ብርድ ሌሊት በተኛሁበት የፍትወት ጠብታ ፈሰሰኝና ከታጠብኩ እንደምጐዳ ስላሰብኩ ተየሙም አድርጌ ጓደኞቼን ሱብሂ አሰገድኩ፡፡” (አህመድ አቡዳውድና ዳረቁጥኒይ)
6. ንፁህ በሆነና ባልተነጀሰ አቧራማ አፈር ማድረግ፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡-
‹‹ንጹሕን የምድር ገጽ አስቡ ፡፡ ከሱም ፊቶቻችሁንና እጆቻችሁን አብሱ፡፡›› (አል ማኢዳህ 6)
ኢብኑ አባስ እንዲህ ብለዋል “
الصعيد ” ማለት የእርሻ አፈር ሲሆን “الطيب ” ደግሞ ጠሃራ የሆነ ማለት ነው፡፡ አፈር ካልተገኘ ግን በጠጠር ወይም በድንጋይ ተየሙም ማድረግም ይቻላል፡፡ ምክንያቱም አላህ እንዲህ ብሏል፡-
‹‹አላህንም የቻላችሁትን ያክል ፍሩት›› (አል ተጋቡን 16)
                                     
                                     ትምህርት ቁጥር 3

                                  #የተየሙም_አፍራሾች

1. ተየሙም ለ“ትንሹ ሀደስ” ተደርጐ ከሆነ እንደ ሽንት ሰገራ ያሉ ውዱእን የሚያበላሹ ተየሙሙን ያበላሹታል፡፡
ለ”ትልቁ ሀደስ” ተደርጐም ከሆነ እንደ ጀናባ፣ የወር አበባና የወሊድ ደም የመሳሰሉት ገላን የሚያሳጥቡ ነገሮች ያበላሹታል፡፡ ምክንያቱም ተየሙም ምትክ በመሆኑ ምትክ የተተካለትን ነገር ድንጋጌ ይይዛልና፡፡
2. ተየሙም በውሃ እጦት ተደርጐ ከሆነ ውሃ ሲገኝ ተየሙም ይፈርሳል ነብዩ (ሠለላሁ ዓለይሒ ወሠለም) እንዲህ ብለዋል
“ውሃ ካገኘህ ግን ገላህን አስነካው (ታጠብ)፡፡”

3. እንደ ህመም የመሳሰሉ ተየሙምን ለመፈፀም ምክንያት የሆኑ ነገሮች ሲወገዱም ተየሙም ይፈርሳል፡፡

                          ትምህርት ቁጥር 4

                        #የተየሙም_አደራረግ

                        የተየሙም አደራረግ

የተየሙም አደራረግ በልብ አስቦ ቢስሚላሂ ካለ በኃላ በሁለት እጆች አንድ ጊዜ መሬትን መታ ማድረግ፣
ከዚያ በመንፋት ወይም በማራገፍ ፊትንና እጆችን እስከ ሰዓት ማሰሪያ ድረስ ማበስ ነው፡፡
ለዚህ ማስረጃው አማር በአስተላለፈው ሀዲስ ውሰጥ ነብዩ (ሠለላሁ ዓለይሒ ወሠለም)
“ተየሙም ለፊትና ለእጆች አንድ ጊዜ መሬትን መምታት ነው” ብለዋል፡፡
በሌላም ሀዲስ ነብዩ (ሠለላሁ ዓለይሒ ወሠለም) ለአማር እንዲህ ብለውታል
“እንዲህ ብታደርግ በቂ ነው” አሉና መሬትን በእጃቸው መታ አድርገው ኡፍ ካሉት በኃላ የእጆቻቸውን ላይና ፊታቸውንም አበሱ፡፡
(ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)


SHARE THIS POST   

  • Facebook
  • Twitter
  • Myspace
  • Google Buzz
  • Reddit
  • Stumnleupon
  • Delicious
  • Digg
  • Technorati
Author: Mohammad
Mohammad is the founder of STC Network which offers Web Services and Online Business Solutions to clients around the globe. Read More →

0 comments: