Download this Blogger Template by Clicking Here!

Ad 468 X 60

Saturday 23 August 2014

Widgets

ጦሓራ




 1 የጦሓራ ትርጉም

ቋንቋዊ ትርጉሙ፡- ጦሓራ የዓረብኛ ቃል ትርጉሙ ከማንኛውም ቆሻሻ መፅዳት ማለት ነው፡፡
ትምህርታዊ ትርጉሙ፡- “ሀደሥን”ና ቆሻሻን ማስወገድ ነው::
“ሀደሥን” ማስወገድ ሲባል ሰላትን የሚከለክልን ባህሪ ከአካል ማውረድ ማለት ሲሆን ትልቁ ከሆነ ሙሉ አካልን ትንሹ ከሆነ ደግሞ የዉዱእ አካሎችን በውሃ በመታጠብ ውሃ ከጠፋ ወይም መጠቀም ካልተቻለ ሸሪዓው ባዘዘው መልኩ አፈርን በመጠቀም ነው፡፡
ቆሻሻን ማስወገድ ሲባል ደግሞ ነጃሳን ከአካል ከልብስና ከቦታ ማስወገድ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አካላዊ ጦሓራ ሁለት አይነት ነው ማለት ነው፡፡
=> “ሀደስን” ማስወገድ አካልን ብቻ የሚመለከት ሲሆን
=>ቆሻሻን ማስወገድ ደግሞ አካልን ልብስንና ቦታን የሚያካትት ነው፡፡
“ሀደስ” ሁለት አይነት ነው፡፡
1=>ትንሹ “ሀደስ” ውዱእን የሚያስገድድና
2=>ትልቁ “ሀደስ” ደግሞ ገላ ትጥበትን የሚያስከትል ነው፡፡
ነጃሳ ደግሞ ሶስት አይነት ነው፡፡
1=>መታጠቡ ግድ የሚሆን፣
2=>ውሃ መርጨት በቂ የሚሆንና
3=>ማበስ ብቻ የሚበቃው ናቸው፡፡
2 የጦሓራ ወሳኝነቱና ክፍሎቹ


የጦሓራ ወሳኝነትና ክፍሎቹ፡-
ጦሓራ የሰላት መክፍቻና ከመስፈርቶቹ አሳሳቢው ነው፡፡ የአንድ ስራ መስፈርት ደግሞ የግድ ከስራው መቅደም አለበት፡፡
ጦሓራ በሁለት ይከፈላል፦
አንደኛው ክፍል፡- ውስጣዊ ፅዳት ሲሆን ልብን ከሽርክ ከኃጢአትና ከማንኛውም ውስጣዊ ጉድፍ ማፅዳት ማለት ነው፡፡ የልብ ፅዳት ከአካል ፅዳት የበለጠ አሳሳቢ ጉዳይ ነው:: እንዲያውም የልብ ቆሻሻ እያለ አካል ሊፀዳ አይችልም፡፡
አላህ እንዲህ ብሏል ፡-
‹‹አጋሪዎች እርኩሶች ብቻ ናቸው፡፡›› (ተውባህ 28)
ሁለተኛው ክፍል አካላዊ ፅዳት፡- ይህ ክፍል ተከታታይ በሆኑ ነጥቦች የሚብራራ ነው፡፡




3 ጦሓራ ሊደረግበት የሚችል ውሃ


ጦሓራ ነጀሳን በማስወገድና “ሀደስን” በማነሳት ጦሓራ ሊደረግበት የሚችል ነገርን ይፈልጋል፡፡ በዋነኝነት ውሃ ነው፡፡
በተገቢው መልኩ ጦሓራ ሊደረግበት የሚችል ውሃ ደግሞ ራሱ ፅዱ ሆኖ ሌላውንም የሚያፀዳ ሲሆን ይህም ተፈጥሯዊ ይዘቱ ላይ ያለ ውሃ ነው፡፡ ይህም ውሃ
=>ከሰማይ የወረደ ለምሳሌ ዝናብ፣ የጤዛ ፍሳሽና የቀለጠ በረዶ ወይም ደግሞ
=>የመሬት ላይ ፈሳሽ እንደወንዞች፣ ምንጮች፣ የጉድጓድ ውሃና ባህር ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህም ማስረጃ አላህ እንዲህ ይላል፡-
‹‹ውሃውንም በእርሱ ሊያጠራችሁ… በእናንተ ላይ ከሰማይ ባወረደላችሁ ጊዜ (አስታውሱ)፡፡›› (አል አንፋል 11)
‹‹ከሰማይም አጥሪ ውሃን አወረድን፡፡››(አል ፉርቃን 48)
ነብዩም (ሠለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል “ጌታዬ ሆይ ወንጀሌን በውሃ በጤዛና በበረዶ እጠበው” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

ስለባህር ውሃም እንዲህ ብለዋል
“ውሃው ንፁህ የሚያፀዳ ነው ሞቱም የተፈቀደ ነው”
(አቡዳውድ፣ቲርሚዚይ፣ነሳኢይና ኢብኑማጃህ ዘግበውታል)

ከውሃ በቀር በሌላ እንደ ቤንዚን፣ ጭማቂ ሎሚ በመሳሰሉት ፈሳሽ ነገሮች ጦሓራን መፈፀም አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አላህ እንዲህ ብሏል፡-
‹‹ውሃን ባታገኙ ንጹሕን የምድር ገጽ አስቡ፡፡›› (አል ማኢዳህ 6)
ከውሃ ውጭ በሌላ ፈሳሽ ነገር ጦሓራ ማድረግ ቢቻል ኖሮ ውሃ ያጣ ሰው ከአፈር ይልቅ ያን አማራጭ እንዲጠቀም ይጠቆም ነበር፡፡




4 ውሃ ከነጃሳ ጋር ሲቀላቀል የሚኖረው ሁኔታ

ውሃ በውስጡ ነጃሳ በመደብለቁ ምክንያት ከሶስቱ ባህሪዎቹ ማለትም :-
1ከሽታው 2ጣዕሙና 3መልኩ
አንዱ ከተቀየረ በሁሉም ዑለማዎች ስምምነት ይህ ውሃ ነጃሳ በመሆኑ አነሰም በዛም ነጃሳን ለማሰወገድም ሆነ “ሀደስን” ለማንሳት እሱን መጠቀም አይፈቀድም፡፡
በተቀላቀለው ነጃሳ ግን ባህሪው ካልተለወጠና ውሃው ብዙ ከሆነ ነጃሳ ስለማይሆን ለጦሓራ መጠቀም ይቻላል፡፡ ነገር ግን ትንሽ ከሆነ ስለሚነጀስ በሱ ጦሓራ ማድረግ አይፈቀድም፡፡
የብዙ ውሃ መጠን ሁለትና ከዚያ በላይ “ቁለት”(በነቢዩ (ሠለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ዘመን የነበረ መለኪያ ሲሆን አንዳንድ የዘመናችን ዑለሞች 160 ሊትር እንደሚሆነ ይናገራሉ::) ሲሆን ትንሹ ደግሞ ከዚያ በታች የሆነ ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃው አቡ ሰዒድ አል ኹድሪይ ያስተላለፉት ሀዲስ ነው፡፡
=>ነብዩ (ሠለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል “ውሃ ንፁህና የሚያፀዳ ሲሆንም በመሆኑ ምንም ነገር አይነጅሰውም፡፡”(አህመድ ዘግበውታል)

=> ኢብኑ ዑመር ባስተላለፉትም ሀዲስ የአላህ መልዕክተኛ (ሠለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል “ውሃ ሁለት ቁለት ከደረሰ ነጃሳን አይይዝም፡፡”(አህመድ ዘግበውታል)
5 ውሃ ከንፁህ ነገር ሲቀላቀል የሚኖረው ሁኔታ

ውሃ ንፁህ የሆነ ነገር ለምሳሌ የዛፍ ቅጠል፣ ሳሙና፣ ሻምፖ፣ ቁርቁራና የመሳሰሉ ንፁህ ነገሮች ቢገባበትና የተደበለቀው ነገር በልጦ ካልተገኘ ከዑለሞች ትክክለኛው አቋም ይህ ውሃ ማፅዳት መቻሉ ስለሆነ ሀደስንና ነጃሳን ሊወገድበት ይቻላል፡፡
አላህ እንዲህ ብሏል፡-
وَإِن كُنتُم مَّرْضَىٰ أَوْ عَلَىٰ سَفَرٍ أَوْ جَاءَ أَحَدٌ مِّنكُم مِّنَ الْغَائِطِ أَوْ لَامَسْتُمُ النِّسَاءَ فَلَمْ تَجِدُوا مَاءً فَتَيَمَّمُوا صَعِيدًا طَيِّبًا فَامْسَحُوا بِوُجُوهِكُمْ وَأَيْدِيكُمْ ۗ إِنَّ اللَّهَ كَانَ عَفُوًّا غَفُورًا [٤:٤٣]
‹‹በሽተኞች ወይም በጉዞ ላይ ብትኾኑም፥ ወይንም ከእናንተ አንዱ ከዓይነምድር ቢመጣ፥ ወይንም ሴቶችን ብትነካኩና ውሃን ባታገኙ፣ ንጹሕ የኾነን የምድር ገጽ አስቡ፡፡ ፊቶቻችሁንና እጆቻችሁንም (በርሱ) አብሱ፡፡ አላህ ይቅር ባይ መሓሪ ነውና፡፡›› (ኒሳእ 43)
በዚህ አንቀፅ ውስጥ በድፍኑ ውሃ ሰለተባለ ይህ ቃል ሁሉንም አይነት ውሃ ይይዛል:: በዚህ መሰረት የጠራና የደፈረሰ ውሃ ለውጥ አይኖረውም፡፡
ነቢዩም (ሠለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የልጃቸውን አስክሬን ላጠቡ ሴቶች እንዲህ ብለዋቸዋል
“እንደመሰላችሁ ሶስት ጊዜ አምስቴ ወይም ከዚያ በላይ በውሃና በቁርቁራ ካጠባችኋት በኋላ መጨረሻው ላይ ካፉር አድርጉ፡፡”
(ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
6 ለንፁህ ነገር ግልጋሎት የዋለ ውሃ ሁክም

ጦሓራ ለሆነ ነገር ግልጋሎት የዋለ ውሃ ለምሳሌ የውዱእ ወይም የገላ ትጥበት እንጥብጣቤ ንፁህና ሌላውነም ማፅዳት የሚችል “ሀደስን”ና ነጃሳንም የሚያስወግድ ነው፡፡
ለዚህም ማስረጃው “ነብዩ (ሠለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ውዱእ ሲያደርጉ ሰሃቦች የርሳቸውን እጣቢ ለማግኘት ይፋጁ ነበር”(ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

እንዲሁም ነብዩ (ሠለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ጃቢር የታመሙ ጊዜ የውዱእ እጣቢያቸውን ረጭተውባቸዋል፡፡ ነጃሳ ቢሆን ኖሮ ይህ አይቻልም ነበር፡፡
እንዲሁም ነብዩ (ሠለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሶሃቦችና ሚስቶቻቸውም በኩባያና በጆግ ውዱእ ያደርጉ ነበር፡፡ በድስት ገላቸውን ይታጠቡ ነበር፡፡ ይህ ሲሆን ውሃው ከእንጥብጣቤ አይድንም፡፡
እንዲሁም ነብዩ (ሠለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ለአቡ ሑረይራ
“ሙእሚን አይነጅስም” ብለውታል” (ሙስሊም ዘግበውታል)
ስለዚህ አንድ ሰው ውሃን በመጠቀሙ ምክንያት ጦሃራነቱ አይወገድም ማለት ነው::
7 የሰውና የቤት እንስሳ ትራፊ

ትራፊ የምንለው አንድ ሰው ከጠጣ በኋላ የሚተርፈውን ነው፡፡ የሰው ልጅ ሙስሊምም ይሁን ከሃዲ ጦሃራ እንደሆነ ሁሉ ትራፊውም ንፁህ ነው፡፡ እንዲሁም “ጀናባ” (ገላ የሚያስታጥብ ነገር) ወይም የወር አበባ ያለባቸውም ለውጥ የላቸውም፡፡
ከሃዲ ነጃሳ መሆኑን የሚናገረውን የቁርአን አንቀፅ ዑለሞች የተረጎሙት ውስጣዊ እምነቱን የሚመለከት እንጂ አካሉ በንክኪ ይነጅሳል ማለት እንዳልሆነ ነው::
የአላህ መልዕክተኛ (ሠለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) “ሙእሚን አይነጅስም” ብለዋል (ሙስሊም ዘግበውታል)
ስጋው የሚበላ እንስሳ ያስተረፈውም ትራፊ በዑለሞች ስምምነት (ኢጅማዕ) መሰረት ንፁህ ነው፡፡ ስጋው የማይበላ እንስሳ ሲሆን ግን ለምሳሌ አውሬ ወይ አህያ ትክክለኛው አቋም ውሃው ብዙ ከሆነ ትራፊያቸው ጦሓራ ሲሆን ትንሽ ከሆነና ከውሃው በመጠጣታቸው ምክንያት ይዘቱን ቢለውጥ ነጃሳ ይሆናል፡፡
ለዚህም ማስረጃ ከላይ እንዳሳለፍነው “ውሃ ሁለት ቁለት ከደረሰ ነጃሳ አይይዝም” በተጨማሪም ነብዩ (ሠለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ድመት ስለጠጣችበት ውሃ ተጠይቀው እንዲህ ብለዋል “ድመት በእናንተ መካከል ተዟዟሪ በመሆኗ ነጃሳ አይደለችም” ደግሞም እንዲህ አይነት እንስሳዎችን መከላከል ስለሚያዳግት የጠጡበትን ውሃ ነጃሳ ማድረግ አላህ ለህዝቡ የማይፈልገው ችግር ውስጥ መግባት ነው፡፡
የውሻና የከርከሮ ትራፊ ግን ነጃሳ ነው ነብዩ (ሠለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል “ውሻ ከእቃችሁ ከጠጣ የሚፀዳው አንዱን በአፈር ቀላቅሎ ሰባት ጊዜ ሲታጠብ ነው፡፡ ከርከሮ ደግሞ ነጃሳ የሆነው ቆሻሻ አፀያፊ ስለሆነ ነው፡፡
አላህ እንዲህ ይላል፡-
« እርሱ ርኩስ ነውና » (አል አንዓም 145)
 

SHARE THIS POST   

  • Facebook
  • Twitter
  • Myspace
  • Google Buzz
  • Reddit
  • Stumnleupon
  • Delicious
  • Digg
  • Technorati
Author: Mohammad
Mohammad is the founder of STC Network which offers Web Services and Online Business Solutions to clients around the globe. Read More →

0 comments: