Download this Blogger Template by Clicking Here!

Ad 468 X 60

Monday 25 August 2014

Widgets

ነጃሳና አይነቶቹ



                              ትምህርት ቁጥር 1

                        #የነጃሳ_ትርጉምና_አይነቶቹ

የነጃሳ ትርጉምና አይነቶቹ

ነጃሳ ማለት ሸሪዓው እንድንርቀው ያዘዘን ማንኛው ፀያፍ አካል ሲሆን ነጃሳ ሁለት አይነት ነው::

1. ግኡዝ አካላዊ ነጃሳ፡- እንዲህ አይነቱን ነጃሳ ነገሩ ራሱ ነጃሳ በመሆኑ ማፅዳት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ደም፣ ሽንትና የመሳሰሉት ማለት ነው::

2. አካል ላይ በማረፍ ሶላትን የሚከለክል ነጃሳ፦ እዚኛው ውስጥ በዉዱእ የሚወገድ ትንሹ ሀደስና በትጥበት የሚወገድ ትልቁ ሀደስ ይካተታል::

ነጃሳን የምናስወግድበት ዋናው አስወጋጅ #ውሃ ነው፡፡ ውሃ እያለ በሌላ ነገር ማፅዳት አይቻልም፡፡ አላህ አንዲህ ይላል፡-
‹‹ውሃውንም በእርሱ ሊያጠራችሁ… በእናንተ ላይ ከሰማይ ባወረደላችሁ ጊዜ (አስታውሱ)፡፡››
(አል አንፋል 11)

ነጃሳ በሶስት ይከፈላል፦

#ከባድ ነጃሳ፡- ይህ ውሻና የእሱ ተዋላጅ ነው፡፡
#ቀላል ነጃሳ፡- ምግብ ያልጀመረ የወንድ ህፃን ልጅ ሽንት ነው፡፡
#መካከለኛ ነጃሳ፡- የተቀሩ ነጃሳዎች በአጠቃላይ ለምሳሌ ሽንት፣ ሰገራና በክት እዚህ ውስጥ ይካተታሉ፡፡
                          
                            ትምህርት ቁጥር 2

                   ነጃሳ ስለመሆናቸው ማስረጃ ያላቸው ነገሮች

1. የሰው ልጅ ሽንትና ደም ፀያፍ ነገሮች ምግብ ያልጀመረ የህፃን ወንድ ሽንት ግን በላዩ ውሃ መርጨት ብቻ በቂ ነው፡፡
ለዚህ ማስረጃው ኡሙ ቀይስ ቢንት ሚህሰን ያስተላለፉት ሀዲስ ነው፦ “ምግም መብላት ያልጀመረ ህፃን ወንድ ልጅ ነብዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ዘንድ አመጣችና እሳቸውም በእቅፋቸው አደረጉት ህፃኑም በነብዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ልብስ ላይ ሲሸና ነብዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ውሃ እንዲመጣ አደረጉና ሳያጥቡት በመርጨት ብቻ ተብቃቁ፡፡” ምግብ የጀመረ የህፃን ወንድና የህፃን ሴት ልጅ ሽንት ግን እንደ አዋቂ ይታጠባል፡፡
2. ስጋው ከሚበላ እንስሳ የሚወጣ ፈሳሽ ደም ነጃሳ ሲሆን ጉሮሮ ወይም ስጋ ላይ የሚቀረው ደም ግን ጦሃራ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡-
‹‹…ወይም ፈሳሽ ደም…›› (አል አንዓም 145)
3. የማንኛውም ስጋው የማይበላ እንስሳ ሽንትና ፈርስ፦ ለምሳሌ የድመትና የአይጥ::
4. በክት፦ ማለትም ሸሪዓዊ በሆነ መንገድ ሳይታረድ የሞተ እንስሳ ከዚህ ውስጥ ግን አሳ፣ አንበጣና ፈሳሽ ደም የሌላቸው ነገሮች ይለያሉ፡፡ እነዚህ ጦሃራ ናቸው::
5. “መዝይ” መዝይ ማለት ቀጭን ነፃ ያለ የዘር ፈሳሽ መሳይ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ በመተሻሸት ወይም ግብረስጋ ግንኙነትን በማሰብ የሚፈስ ነው፡፡ አፈሳሰሱ ግን በሀይልና በስሜት አይደለም፡፡ እንዲሁም ከፈሰሰ በኋላ ድካም ካለመሰማቱም በላይ መፍሰሱም ላይታወቅ ይችላል፡፡ ይህ ፈሳሽ ነጃሳ ለመሆኑ ማስረጃው ነብዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በዚህ ጉዳይ ላይ ለዓልይ እንዲህ ማለታቸው ነው
“ውዱእ አድርግ ሀፍረተ ገላህንም ውሃ አፍስስበት፡፡”(ቡኻሪ ዘግበውታል)
እንዲታጠብ ያላዘዙት ይህን ፈሳሽ መራቅ ስለማይቻል ለማግራራት ሲሉ ነው፡፡
6. “ወድይ” ይህም ነጣ ያለና ወፈር የሚል ፈሳሽ ሲሆን ከሽንት ተከትሎ የሚፈስ ነው፡፡
7. የወር አበባ ደም፦ አስማእ ቢንት አቢበክር እንዳስተላለፉት “አንዲት ሴት ወደ ነብዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በመምጣት እንዲህ በማለት ጠየቀቻቸው “የወር አበባ ደም ልብሳችንን ሲነካው እንዴት ነው የምናደርገው?” እሳቸውም እንዲህ ብለው መለሱ
“በደረቁ ትፈግፍገው ከዚያ በውሃ ቆንጠር አድርጋ ትሸው ከዚያ ሙሉ በሙሉ ትጠበውና ትስገድበት፡፡” ( ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
                           
                              ትምህርት ቁጥር 3

                      ነጃሳን እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል

1. ነጃሳው መሬት ወይም ቦታ ላይ ከከሆነ የነጃሳውን እይታ በሚያስወግድ መልኩ አንድ ጊዜ ውሃ ከተደፋበት በቂ ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃው ነብዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) መስጂድ ላይ አንድ የገጠር ሰው ስለሸና ውሃ እንዲፈስበት ማዘዛቸው ነው:: (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
2. መሬት ላይ ካልሆነና ለምሳሌ ልብስ ወይም ዕቃ ላይ ከሆነ ውሻ አፉን የከተተበት እቃ ሰባት ጊዜ አንዱን በአፈር ቀላቅሎ ማጠብ ሲሆን ማስረጃው፦
ነብዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) “እቃችሁ ላይ ውሻ አፉን ከነከረ ሰባት ጊዜ አንዱን በአፈር አድርጋችሁ እጠቡ::”(ሙስሊም ዘግበውታል)
የነጀሰው ከሆነ ግን ከዑለማዎች አቋሞች ትክክለኛው አንድ ጊዜ ብቻ ነጃሣውን የሚያስወግድ እጥበት ማጠብ ነው፡፡ በመሆኑም ሰባት ጊዜ ማጠብ አያስፈልገውም፡፡
የሽንት የሰገራ የደምና የመሳሰሉት ነጀሳ ከሆነ አንድ ጊዜም ቢሆን በደብም አሽቶ በማጠብና በመጭመቅ እስኪወገድ ድረስ ማፅዳት በቂ ነው፡፡
ምግብ መብላት ያልጀመረ የወንድ ህፃን ልጅ ሽንት ግን ውሃ ላዩ ላይ መርጨት በቂ ነው፡፡
ማስረጃውም፦ “የሴት ህፃን ልጅ ሽንት መታጠብ አለበት የወንድ ህፃን ሽንት ግን ውሃ መርጨት በቂ ነው፡፡” (አቡዳውድ ነሳኢይና ኢብን ማጃህ ዘግበውታል) የሚለው ሀዲስ ነው::
ከላይ ያሳለፍነው ኡሙ ቀይስ ቢንት ሚህሰን ያስተላለፉትም ሀዲስ ለዚህ ማስረጃ ሊሆን ይችላል፡፡
ስጋው የሚበላ እንስሳ የበክቱን ቆዳ በማልፋት ጦሃራ ማድረግ ይቻላል፡፡ ነብዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል “የሞተ እንስሳ ቆዳ በማልፋት ጦሃራ ይሆናል፡፡”(ነሳኢይ ቲርሚዚይና ኢብኑ ማጃህ)
የወር አበባ ደም ደግሞ ቆንጥራ ከፈተገችው በኋላ አጥባው ልትሰግድበት ትችላለች፡፡
በጥቅሉ አንድ ሙስሊም ነጃሳን ከቦታ ከአካሉና ከልብሱ በማፅዳት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ለሰላቱ ቅድመ መስፈርት ነው፡፡

SHARE THIS POST   

  • Facebook
  • Twitter
  • Myspace
  • Google Buzz
  • Reddit
  • Stumnleupon
  • Delicious
  • Digg
  • Technorati
Author: Mohammad
Mohammad is the founder of STC Network which offers Web Services and Online Business Solutions to clients around the globe. Read More →

0 comments: