Download this Blogger Template by Clicking Here!

Ad 468 X 60

Tuesday 26 August 2014

ሰላት



                                 ትምህርት ቁጥር 1

                                   #ሰላት

                                ክፍል አንድ

1.
ትርጉሙ፦
ሰላት የዓረብኛ ቋንቋ ትርጉሙ ድዓእ (ልመና) ማለት ሲሆን
ሸሪዓዊ ትርጉሙ ደግሞ፦ በተክቢራ የሚጀመርና በማሰላመት የሚጠናቀቅ ለየት ያሉ ንግግሮችና ተግባሮች ማለት ነው፡፡
2.
ትሩፋቱ፦
ሰላት ከሁለቱ የምስክር ቃሎች ቀጥሎ ከባዱ የኢስላም ማዕዘን ከመሆኑም በላይ የኢስላም ዋናው
መሰረት ነው፡፡ አላህ ነብዩን ወደ ሰማይ በማሳረገ ከሰባቱ ሰማይ በላይ እያሉ ይህን ሰላት መደንገኑ በሙስሊሞች ህይወት ላይ ሰላት ወሳኝ ነገር መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ነብዩም አንዳች ነገር ሲገጥማቸው ቶሎ ወደ ሰላት ይሮጡ ነበር፡፡ ስለ ሰላት ትሩፋት የሚገልፁ ሀዲሶች በጣም ብዙ ቢሆኑም የተወሰነውን ብቻ እነሆ፡-
ነብዩ () እንዲህ ብለዋል
አምስቱ ሰላቶች ከጁምዓ እስከ ጁምዓ ከረመዳን እስከ ረመዳን ታላላቅ ወንጀሎችን ሲቀር በመካከላቸው ያሉትን ኃጢአቶች የሚያብሱ ናቸው::”(ሙስሊም ዘግበውታል)

በሌላም ሀዲስ እንዲህ ብለዋል
እስቲ ንገሩኝ በደጃፋችሁ ወንዝ ቢኖርና በቀን አምስት ጊዜ በትታጠቡ እድፍ ሊኖርባችሁ ይችላል? ሰሃቦችምአይኖርምሲሉይህ የአምስቱ ሰላቶች ምሳሌ ነው አላህ በእነሱ ሰበብ ኃጠአቶችን ያበሳልአሉ:: (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
ግዴታ ስለመሆኑ፡-

ሰላት ግዴታ መሆኑ በቁርአን በሀዲስና በዑለማዎች ስምምነትም (ኢጅማዕ) የተረጋገጠ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡-
‹‹ሶላትንም ደንቡን ጠብቃችሁ ስገዱ፡፡›› (አል በቀራህ 43)
በዚህ መልኩ በብዙ አንቀፆች ላይ ተናግሯል፡፡
በሌላም አንቀፅ አላህ እንዲህ ብሏል፡-
‹‹ለእነዚያ ላመኑት ባሮቼ በእርሱ ውስጥ ሽያጭና ወዳጂነት የሌለበት ቀን ከመምጣቱ በፊት ሶላትን በደንቡ ይሰግዳሉ፡፡›› (አል ኢብራሂም 31)

ከሀዲስ ማስረጃዎች ውሰጥም ነብዩ (
) እንዲህ ብለዋል
“ሰላቶች አምሰት ምንዳቸው ግን ሀምሳ ነው፡፡”(ቡኻሪ ዘግበውታል)
ቡኻሪና ሙሰሊም በዘገቡት ሀዲስ ስለ ኢስላም ለጠየቃቸው ግለሰብ እንዲህ ብለውታል
“በቀንና በሌሊት ውስጥ አምስት ሰላቶችን መስገድ…” ጠያቅውም ከዚህ ሌላ አለብኝን? ሲላቸው አይ በራስህ ፈቃድ ከሰገድክ እንጂ ሌላ ግዴታ ሰላት የለምብህም ብለውታል፡፡”

ሰላት ግዴታ የሚሆነው አቅመ አዳም በደረሰና አእምሮ ጤናማ በሆነ ሙስሊም ላይ ሲሆን ካፊር ህፃንና እብድ ላይ ግዴታ አይደለም፡፡ ነብዩ እንዲህ ብለዋል
“ከሶስት ሰዎች ብዕር ተነስቷል (ወንጀል አይፃፍባቸውም ማለት ነው) የተኛ እስኪነቃ፣ እብድ እስኪድንና ህፃን እስኪደርስ፡፡”

ህፃን ሰባት አመት ሲሞላው ሶላት እንዲሰግድ መታዘዝ ሲኖርበት አስር አመት ሞልቶት ማይሰግድ ከሆነ ደግም በመግረፍ እንዲሰግድ ማድረግ ግዴታ ነው፡፡ የሰላትን ግዴታነት የካደ ወይም የማይሰግድ በዚህ ተግባሩ ከእስልምና ይወጣና ከሀዲ ይሆናል፡፡
ነብዩ እንዲህ ብለዋል
“በእኛና በእነርሱ መካከል ያለው መለያ ሰላት ነው እሱን የተወ በእርግጥ ክዷል፡፡” (ሙስሊም ዘግበውታል)

                                 ትምህርት ቁጥር 2

                                 #የሰላት_ወቅቶች

                                 የሰላት ወቅቶች

ግዴታ የሆኑ ሰላቶች በሀያ አራት ሰዐት ውስጥ አምስት ሲሆኑ ለእያንዳንዱ ሰላት የተወሰኑ ወቅቶች አሏቸው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡-

‹‹ሶላት በምእምናን ላይ በጊዜያት የተወሰነች ግዴታ ናትና፡፡›› (አል ኒሳእ:1ዐ3)
በመሆኑም ወቅቱ ሳይደርስ የሚሰገድ ሰላት ተቀባየይነት የለውም፡፡
ስለ ሰላት ወቅት ከሚጠቅሱ ሀዲሶች ዋናው ኢብኑ ዑመር ያስተላለፉት ሀዲስ ሲሆን
ነብዩ (
)እንዲህ እንዳሉ አስተላልፈውልናል :-

“የዙህር ወቅት ፀሐይ ወደ ምዕራብ ዘንበል ካለችበት ሰዓት ጀምሮ የአንድ ሰው ጥላ ከቁመቱ እኩል ሊሆን ትንሽ እስኪቀረው ድረስ ነው፡፡
የዓስር ወቅት ደግሞ የፀሐይ ጥላ ከአንድ ሰው ቁመት እኩል ከሚሆንበት ሰዓት ጀምሮ ፀሐይ ደብዘዝ እስክትል::
የመግሪብ ወቅት ፀሐይ ከጠለቀችበት ሰዓት ጀምሮ የሰማይ ደንገዝገዝ እስኪሰወር::
የዒሻ ወቅት ደግሞ እስከ እኩለ ለሊት ድረስ ሲሆን
የሱብሂ ሰላት ወቅት ደግሞ ጐህ ከቀደደ ጀምሮ ፀሐይ ልትወጣ ትንሽ እስከሚቀራት ድረስ ነው፡፡”(ሙስሊም ዘግበውታል)

                                የዙህር ወቅት

የዙህር ወቅት ፀሐይ ከእኩለ ሰማይ ወደ ምዕራብ ዘንበል ስትል ጀምሮ የአንድ ነገር ጥላ ከርዝመቱ እኩል እስከሚሆን ድረስ ሲሆን በመጀመሪያው ወቅት ላይ መስገድ ግን የተወደደ ነው፡፡ ነገር ግን ጠራራ ፀሐይ ከሆነ ትንሽ በረድ እስከሚል ድረስ ማዘግየት የበለጠ ይወደዳል፡፡ ነብዩ እንዲህ ብለዋል
“ሙቀት ከፍተኛ ሲሆን ትንሽ በረድ አድርጋችሁ ዙህርን ስገዱ ከፍተኛ ሙቀት የጀሀነም እንፋሎት ነው፡፡”(ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

                             የዐስር ሰላት ወቅት

የዐስር ሰላት ወቅት የአንድ ነገር ጥላ ከቁመቱ እኩል ከሆነበት ማለትም ከዙህር ማብቂያ ወቅት ጀምሮ ፀሐይ ሊጠልቅ ትንሽ እስከሚቀረው ድረስ ሲሆን ዐስርንም በመጀመሪያው ወቅት መስገድ ሱና ነው፡፡ እንዲያውም መካከለኛይቱ ሰላት በማለት አላህ እንዲህ ሲል የገለፀው ነው፡-
‹‹በሶላቶች (በተለይ) በመካከለኛይቱም ሶላት ላይ ተጠባበቁ፡፡ ታዛዦች ኾናችሁም ለአላህ ቁሙ፡፡›› (አል በቀራህ 238)
ነብዩም (
) እንድንከባከበው እንዲህ በማለት አዘዋል
“የዐስር ሰላት ያመለጠው ቤተሰቦቹንና ንብረቱን እንዳጣ ነው፡፡”(ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
በሌላም ሀዲስ እንዲህ ብለዋል
“የዐስር ሰላትን የተወ ሰው ስራው ይታበስበታል፡፡”( ቡኻሪ ዘግበውታል)
የመግሪብ ሰላት ወቅት

የመግሪብ ሰላት ወቅት ፀሐይ ከጠለቀበት ሰዓት ጀምሮ ደንገዝ እስከሚል (ፀሀይ መጥለቂያ ጋር የሚኖረው የሰማይ ቅላት እስከሚሰወር) ሲሆን መግሪብንም በመጀመሪያው ወቅት ላይ መስገድ ሱና ነው፡፡ ነብዩ (
) እንዲህ ብለዋል
“ህዝቦቼ መግሪብን ከዋክብት እስኪጠላለፉ ድረስ ካላዘገዩ በመልካም ላይ ናቸው፡፡” (አህመድ አቡዳውድና ሃኪም ዘግበውታል)
የሐጅ ተግባር ላይ ያለ ሰው ግን የሙዝደሊፋን ሌሊት መግሪብን ወደ ዒሻ አዘግይቶ ከዒሻ ጋር መስገዱ የተወደደ ተግባር ነው፡፡
 
                                 የዒሻ ሰላት ወቅት

የዒሻ ሰላት ወቅት ደግሞ እስከ እኩለ ለሊት የሚቆይ ሲሆን ዒሻን ግን አስቸጋሪ ካልሆነ አዘግይቶ በመጨረሻው ወቅት መስገድ ይበልጥ የተወደደ ነው፡፡ ከዒሻ በፊት መተኛትና ከዒሻ በኋላ ደግሞ ወሬ ማውራት የተጠላ ነው::
አቡ በርዛህ ባስተላለፉት ሀዲስ
“ነብዩ ከዒሻ በፊት መተኛትና ከዒሻ በኃላ ማውራት ይጠሉ ነበር::”(ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

                                   የሱብሂ ሰላት ወቅት

የሱብሂ ሰላት ወቅት ደግሞ ጐህ ከቀደደ ጀምሮ ፀሐይ እስክትወጣ ድረስ ሲሆን የጐህ መቅደድ እንደተረጋገጠ ወዲያው መስገድ የተወደደ ነው፡፡
እነዚህ ለሰላት የተደነገጉ ወቅቶች በመሆናቸው ማንኛውም ሙስሊም የሰላት ወቅቶችን እየተጠባበቀ ሳያዘገይ በተወሰነላቸው ወቅቶች ሊሰግድ ይገባል፡፡ አላህ ሰላትን የሚያዘገዩን ሰዎች እንዲህ በማለት ዝቶባቸዋል፡-
‹‹ወዮላቸው ለሰጋጆች፡፡ ለእነዚያ እነርሱ ከስግደታቸው ዘንጊዎች ለኾኑት፤ (ሰጋጆች)፡፡›› (አል ማዑን 4-5)
በሌላ አንቀፅም እንዲህ ብሏል፦
‹‹ከእነሱም በኋላ ሶላትን ያጓደሉ (የተዉ) ፍላጎቶችንም የተከተሉ መጥፎ ምትኮች ተተኩ! የገሀነምንም ሸለቆ በእርግጥ ያገኛሉ፡፡›› (መርየም 59)
ሰላቶችን በወቅቶቻቸው መስገድ አላህ ዘንድ በጣም ከሚወደዱና ብልጫ ካላቸው ስራዎች የሚመደብ ነው፡፡ ነብዩ (
) አላህ ዘንድ በጣም የሚወደድን ስራ ሲጠየቁ
“ሰላቶችን በወቅቶቻቸው መስገድ” በማለት መልሰዋል:: (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
                         
                                  ትምህርት ቁጥር 3

                          #የግዴታ_ሰላቶች_ብዛት

ግዴታ የሆኑ ሰላቶች አምስት ሲሆኑ እነሱም ሱብሂ፣ ዙህር፣ ዐስር፣ መግሪብና ዒሻ ናቸው፡፡ በዚህ ላይ ዑለማዋች ሁሉ የተስማሙ ሲሆን ማሰረጃው ጠልሃ ኢብን ኡበይዲላህ ያስተላለፉት ሀዲስ ነው፡፡

“አንድ ገጠሬ ዓረብ ወደ ነብዩ (
) በመምጣት “አላህ ግዴታ ያደረገብኝ ሰላቶች ስንት ናቸው? በማለት ሲጠይቃቸው እሳቸውም “በቀንና ሌሊት ውሰጥ አምስት ሰላቶችን መስገድ ነው” በማለት መለሱለት::
(ሙስሊም ዘግበውታል)

አነስ ባስተላለፉትም ሀዲስ :-

“ከገጠር አንዱ ወደ ነብዩ (
) መጣና “የእርሶ መልዕክተኛ በቀንና ሌሊት አምስት” ሰላቶችን መስገድ እንዳለብን ነግሮናል” ሲላቸው እሳቸው “እውነቱን ነው” በማለት መለሱለት፡፡(ሙስሊም ዘግበውታል)

                        #የግዴታ_ሰላት_የሚመለከተው_ሰው

ሰላት ግዴታ የሚሆነው በማንኛውም ሙስሊም አቅመ አዳም በደረሰና አእምሮው ጤናማ በሆነ ሰው ሲሆን ህፃን ልጅ ግን ሰባት አመት ሲሞላው እንዲሰግድ መታዘዝ ሲኖርበት አስር አመት ሲሞላው ማይሰግድ ከሆነ በመግረፍ እንዲሰግድ ማድረግ ግዴታ ነው፡፡

ነብዩ (
) እንዲህ ብለዋል
“ልጆቻችሁ ሰባት አመት ሲሞላቸው እንዲሰግዱ እዘዟቸው አስር አመት ሞልቷቸው አልሰግድም ካሉ ግረፏቸው እንዲሁም በመኝታ ለዩዋቸው::” (አህመድ አቡዳውድና ቲርሚዚይ)

SHARE THIS POST   

  • Facebook
  • Twitter
  • Myspace
  • Google Buzz
  • Reddit
  • Stumnleupon
  • Delicious
  • Digg
  • Technorati
Author: Mohammad
Mohammad is the founder of STC Network which offers Web Services and Online Business Solutions to clients around the globe. Read More →

0 comments:

አዛንና ኢቃም



                                   ትምህርት ቁጥር 1

                                    #አዛንና_ኢቃም

የአዛንና ኢቃም ትርጉሞችና ሸሪዓዊ ድንጋጌዎቻቸው

. የአዛንና የኢቃም ትርጉም፦

አዛን ማለት የዓረብኛ ቋንቋ ትርጉሙ ማሳወቅ ማለት ነው፡፡
አላህ እንዲህ ብሏል፡-
ይህ) ከአላህና ከመልክተኛው በታላቁ ሐጅ ቀን የወጣ ወደ ሰዎች የሚደርስ ማስታወቂያ ነው”(9:3)

ሸሪዓዊ ትርጉሙ፦ በተወሰኑ ዚክሮች የሰላት ወቅት መድረሱን ማሳወቅ ማለት ነው፡፡
ኢቃማ ማለት ደግሞ የዓረብኛ ቋንቋ ትርጉሙ የተቀመጠን ማስነሳት ማለት ሲሆን ሸሪዓዊ ትርጉሙ በሚታወቁ ዚክሮች ለሰላት እንዲቆም የሚደረግ ጥሪ ማለት ነው፡፡

. ሸሪዓዊ ድንጋጌያቸው፦
አዛንና ኢቃም ለአምስት ሰላቶች ወንዶች ላይفرض كفاية” (በተወሰኑ ሰዎች ላይ ብቻ ግዴታ) የሆነ ሲሆን በቂ ሰው ከፈፀመው ግዴታነቱ ከሁሉም ይነሳል፡፡

ሁለተኛ

ትክክለኛ እንዲሆኑ መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች
1.
ሙስሊም መሆን፡- ካፊር ቢፈፅማቸው ትክክለኛ አይሆኑም
2.
አእምሮ ጤናማ መሆን፡- ልክ እንደሌሎች አምልኮቶች እብድ በስካር ላይ ያለና ህፃን ቢፈፅማቸው ትክክል አይሆኑም፡፡
3.
ወንድ መሆን፡- ሴት ድምጿ ፈታኝ በመሆኑ አዛን ማድረግ የለባትም፡፡ እንዲሁም ፍናፍንት ከሆነ ወንድነቱ ስለማይታወቅ አዛንና ኢቃም ማድረግ የለበትም፡፡
4.
አዛኑን በሰላት ወቅት ማድረግ፡- ለሱብሂና ለጁምዓ የመጀመሪያዎች አዛን ካልሆነ በቀር የሰላት ወቅት ሳይደርስ አዛን ማድረግ አይፈቀድም፡፡ ኢቃም የሚደረገው ደግሞ ሰላት ውስጥ ለመግባት ሲፈለግ መሆን አለበት፡፡
5.
አዛንና ኢቃም ሲደረግ ቅደም ተከተላቸውን የጠበቀ ተከታታይ የሆኑ ቃላቶች መሆን አለባቸው፡፡ የአደራረጉ ሁኔታ አራተኛው ነጥብ ላይ ይገለፃል፡፡
6.
አዛንና ኢቃም ሸሪዓው በደነገጋቸው ቃላቶችና በዓረብኛ ቋንቋ መደረግ አለባቸው፡፡

                            ትምህርት ቁጥር 2

               #አዛን_አድራጊው_ሊላበሳቸው_የሚወደዱ_ባህሪዎች

1. እውነተኛና ታማኝ ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ለሰላትና ለፆም የሚመረኮዙት በመሆኑ እንዲህ ካልሆነ በአዛኑ ሊያሳስታቸው ይችላል::
2. አቅመ አዳም የደረሰና አእምሮ ጤናማ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን የሚለይ ህፃን ልጅ አዛን ቢል ትክክል ይሆናል፡፡
3. የሰላት ወቅቶችን የሚያውቅ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪዎች መቅቶችን እየተጠባበቀ አዛን ስለሚያደርግ ነው:: የማያውቅ ከሆነ ግን ሊሳሳት ወይም ሊያበላሽ ይችላል::
4. ድምፁ ከፍተኛ ሆኖ ሰዎችን ሊያሰማ የሚችል መሆን አለበት፡፡
5. ከትልቁም ሆነ ከትንሹ ሀደስ የፀዳ መሆን አለበት፡፡
6. ቆሞ ወደ ቂብላ በመዞር አዛን ማድርግ አለበት፡፡
7. ጣቶችን ጆሮው ውስጥ ከትቶ
حي على الصلاة” ሲል ወደ ቀኝ
حي على الفلاح” ሲል ደግሞ ወደ ግራ እየዞረ ማድረግ አለበት፡፡
8. አዛንን ቀስ እያለና ክፍተት እየፈጠረ ኢቃምን ደግሞ እያፋጠነና እያከታተለ ማድግ አለበት፡፡

                             #የአዛንና_የኢቃም_አደራረግ

በሀዲስ ጥቅሶች የተዘገቡ የአዛንና የኢቃም አደራረጐች ብዙ ናቸው፡፡ ከነዚህም ውሰጥ ነብዩ (
) ለአቢ መህዙር የአስተማሩት አደራረግ እንደሚከተለው ነው፡፡
“አሏሁ አክበር አሏሁ አክበር አሏሁ አክበር አሏሁ አክበር፣
አሽሐዱ አንላኢላሃ ኢለሏህ አሽሐዱ አንላኢላሃ ኢለሏህ
አሽሐዱ አነ ሙሐመደ ረሱላሏህ አሽሐዱ አነ ሙሐመደ ረሱላሏህ
ሀየ ዓለ ሰላት ሀየ ዓለ ሰላት
ሀየ ዓለል ፈላህ ሀየ ዓለል ፈላህ
አሏሁ አክበር አሏሁ አክበር
ላኢላሃ ኢለላህ”

                                #የኢቃም_አደርረግ ደግሞ

“ አሏሁ አክበር አሏሁ አክበር፣
አሽሐዱ አንላኢላሃ ኢለሏህ
አሽሐዱ አነ ሙሐመደ ረሱላሏህ
ሀየ ዓለ ሰላት
ሀየ ዓለል ፈላህ
ቀድ ቃመቲ ሰላት ቀድ ቃመቲ ሰላት
አሏሁ አክበር አሏሁ አክበር ላኢላሃ ኢለላህ”
ለዚህ ማሰረጃው አነስ ባስተላለፉት ሀዲስ እንዲህ ብለዋል
“ቢላል አዛን ሲያደርግ ጥንድ ጥንድ እንዲያደርግ ኢቃም ሲያደርግ ደግሞ “ቀድ ቃመቲ ሰላት” ሲቀር ሌሎችን በነጠላ እንዲያደርግ ታዟል፡፡”(ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
ይህ የአዛንና የኢቃም አደራረግ ቢላል ከነብዩ (
) ሀገሩ ጉዞም ላይ ሲሆን የሚያደርገው በመሆኑ የተወደደ አደራረግ ነው፡፡ አዛን ሲደረግ በተርጂዕ(አዛን ላይ የምስክር ቃሎችን ሲናገር አስቀድሞ ለራሱ ብቻ በሚሰማ መልኩ ካለ በኋላ በመጮህ መድገም ነው፡፡) ኢቃም ደግሞ በጥንድ ቢደረግ ችግር የለውም፡፡ ምክንያቱም እንዲህ አይነቱ ልዩነቶች የተፈቀዱ ናቸው፡፡ የሱብሂ አዛን ላይ “ሀየ አለል ፈላህ” ከተባለ በኋላ “አሰላቱ ኸይሩ ሚነ ነውም” ሁለት ጊዜ ማለት ሱና ነው፡፡ምክንያቱም አቡ መህዙም ባስተላለፉት ሀዲስ ነብዩ () እንዲህ ብለዋል:- “ለሱብሂ ሰላት አዛን ስታደርግ “አሰላቱ ኸይሩ ሚነ ነውም” በል፡፡”
                             ትምህርት ቁጥር 3

              #አዛን_አድማጭ_የሚለውና #ከአዛን_በኋላ_የሚደረግ_ድዓ

አዛን አድማጭ የሚለውና ከአዛን በኋላ የሚደረግ ድዓ
አዛን ሲደረግ የሚያዳምጥ ሰው አዛን አድራጊው የሚለውን ቢል የተወደደ ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃው
አቡ ሰዒድ ባስተላለፉት ሀዲስ ነብዩ (
) እንዲህ ብለዋል
“አዛን ስትሰሙ አዛን አድራጊው የሚለውን በሉ፡፡”(ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
“ሀየ አለ ሰላት” እና “ሀየ ፈለል ፈላህ” ሲል ግን አድማጭ “ላሀውለ ወላ ቁወተ ኢለ ቢላህ” (ከአላህ እገዛ ውጭ ብልሀትም ሆነ አቅም የለም ማለት ነው፡፡) ማለት አለበት፡፡
አዛን አድራጊው የሱብሂ አዛን ውስጥ “አሰላቱ ኸይሩ ሚነ ነውም” ሲልም አድማጭ በተመሳሳይ እራሱ ያለውን ይላል፡፡ ይህን ማድረግ ለአዛን እንጂ ለኢቃም አይፈቀድም፡፡ በመጨረሻም ነብዩ (
) ላይ አላህ ሰላትና ሰላምን እንዲያወርድ ከለመነ በኋላ የሚከተለውን ይላል

اللهم رب هذه الدعوة التامة والصلاة القائمة آتي محمدا الوسيلة والفضيلة وابعثه مقاما محمودا

“አሏሁመ ረበ ሀዚሂ ደዕወቲ ታማህ ወሰላቲል ቃኢማህ አቲ ሙሐመደን አልወሲለተ ወልፈሊላህ ወብዐስሁ መቃመን መህሙዳህ”(ቡኻሪ ዘግበውታል)

ትርጉሙም (ጌታዬ ሆይ የዚህ ሙሉዕ ጥሪ ጌታ ሆይ የቆመው ሰላት ጌታ ሆይ ለሙሐመድ ወሲላንና(ነቢዩ እንዲህ ሲሉ ተርጉመውታል “ጀነት ውስጥ ለአንድ ሰው ብቻ የተወሰነ ልዩ ማዕረግ ነው እኔ እንድሆን እመኛለው”) ብልጫን ለግስ እንዲሁም ምስጉን ማዕረግ ላይ አድርጋቸው፡፡) ማለት ነው

SHARE THIS POST   

  • Facebook
  • Twitter
  • Myspace
  • Google Buzz
  • Reddit
  • Stumnleupon
  • Delicious
  • Digg
  • Technorati
Author: Mohammad
Mohammad is the founder of STC Network which offers Web Services and Online Business Solutions to clients around the globe. Read More →

0 comments: